ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ተማሪዎችን አስመረቀ

28 Jul, 2025

ሐምሌ 18/2017 ዓ.ም (ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ) የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ እና የእንስሳት ህክምና ትምህርት ቤት በህክምና ዘርፍ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ 93 የህክምና ዶክተሮች፣ 2 ስፔሻሊቲ፣ 2 የጤና ሳይንስ፣ 31 የእንስሳት ህክምና ዶክተሮችን ጨምሮ 37 የማዕረግ እና 1 የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን በድምሩ 166 ተማሪዎችን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መልካሙ አብቴ በተገኙበት በጥበብ የመሰብሰቢያ አዳራሽ በደመቀ ሁኔታ አስመርቋል፡፡

በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር መንገሻ አየነ ለተመራቂዎች የፈተና ወንዞችን አቋርጣችሁ፤ የፅናት መስዋትነትን ተራራ ወጥታችሁ፤ ቀጣዩን የህይወት ምዕራፍ ለመጀመር ወሳኝ ቀን ላይ ስለደረሳችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ አክለውም የሀኪም ልብ ወደማገገሚያ መንገድ የሚያመራ መብራት ነው ያሉ ሲሆን ዛሬ ካለንበት ሁለንተናዊ የቀውስና ግጭት አዙሪት ለመውጣት ወደ ማገገሚያ የሚያመራው የሀኪም ልብ ዛሬ በፅኑ የሀገራችን ሁኔታ ውስጥ ባለንበት መከራ ለሁሉም መድሃኒት ለመሆን እና መድሃኒትነታችሁ በህክምና ተቋማት የተቀነበበ እና በእንስሳት ህክምና ብቻ የታጠረ ባለመሆኑ ሁለንተናዊ ምላሸ ለመስጠት በፅኑ መሰረት ላይ መቆማችሁን እንደ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እናምናለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ህንፃ በእጅ ይሰራል ቤት ግን በብርቱ ልብና ሩህሩህ ልቦች ይገነባል ያሉት ፕሬዚዳንቱ እነዚህ ወጣት ዶክተሮች እና የእንስሳት ሐኪሞች ከፍ እንዲሉ የሚያስችል የፍቅርና የድጋፍ የርህራሔን ቤት ገንብታችኋል ዩኒቨርሲቲው መስዋዕትነታችሁን ሳያመሰግን አያልፍም ሲሉ የተመራቂ ወላጆችን አመስግነዋል፡፡

ውድ ተመራቂዎች የተለያዩ የሙያ ዘርፍ ወክላችሁ ብትመረቁም የጋራ ተልዕኳችሁ ግን ህዝብን ማገልገል እና አመራር መስጠት ስኬታማ መሆን ብቻ ሳይሆን ተፅዕኖ ፈጣሪ እና የህይወት ዘመን ተማሪ እንድትሆኑ እና በቅንነት እና በርህራሄ ሀገራችሁን እና ህዝባችሁን እንድታገለግሉ ሲሉ ዶ/ር መንገሻ ለተመራቂዎች መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው መልእክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መልካሙ አብቴ በበኩላቸው የዛሬ ተመራቂ የህክምና ዶክተሮች የዓመታት ጽናትን ውጤት፣ ብርታትን፣ ጠንክሮ መስራትን፣ ትምህርትን፤ የለውጥ መሳሪያነት እና የወደፊት የሀገራችን የጤናውን ዘርፍ መፃኢ እድል መወሰኛ ጭምር ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በሀገራችን አሁን ላይ ጤናን መሰረት ባደረገ መልኩ እየተሠራ ባለበት ወቅት መመረቃቸው መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር እና ለጤናው ዘርፍ አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑንም ተናግረዋል።

በክህሎት እና በአመለካከት ቀርጾ እዚህ ደረጃ ላደረሳችሁ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አምባሳደር ናችሁ ያሉት ዶ/ር መልካሙ አብቴ ተመራቂዎች በቆይታቸው የጨበጡትን ክህሎት እና የቀሰሙትን ዕውቀት ተጠቅመው ሀገራቸውን እና ሕዝባቸውን በቅንነት እና በፍጹም ታማኝነት እንድታገለግሉ ሲሉ ለተመራቂዎች መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመጨረሻም ከህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ እንዲሁም ከእንስሳት ህክምና ትምህርት ቤት ተመራቂ ዶክተሮች ውስጥ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ዶ/ር ቤተልሄም እውነቱ እና ዶ/ር ደረበው መኩሪያ የዋንጫ፣ የሜዳሊያ እና የሰርተፊኬት ሽልማታቸውን ከእለቱ የክብር እንግዳ ከዶ/ር መልካሙ አብቴ እና ከዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ከዶ/ር መንገሻ አየነ እጅ ተቀብለዋል፡፡

cong11cong2cong3