
አስራ ሁለተኛው የሂሳብ ካምፕ መርሃ-ግብር ተጀመረ
29 Jul, 2025
አስራ ሁለተኛው የሂሳብ ካምፕ መርሃ-ግብር ተጀመረ፡፡
ሐምሌ 21/2017 ዓ.ም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከሚሰጠው የማህበረሰብ አገልግሎት አንዱ የሆነው እና በየአመቱ በክረምት የሚካሄደው 12ተኛው የሂሳብ ካምፕ መርሃ ግብር ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች ተመርጠው የመጡ የ10ኛ እና 11ኛ ክፍል ተማሪዎች፣ የሳይንስ ኮሌጅ መምህራን እንዲሁም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አመራሮች በተገኙበት በዩኒቨርሲቲው ፔዳ ግቢ ተጀምሯል፡፡
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሂሳብ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ዶ/ር ሁነኛው ደሴ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው ተማሪዎች ወደ ካምፑ ለመቀላቀል የተመለመሉበት መስፈርት በትምህርት ቤታቸው ባላቸው ከፍተኛ ውጤት እና መልካም ባህሪ መሆኑን ገልጸው የመርሃ ግብሩ ዓላማ ሂሳብን በጨዋታ መልክ በማስተማር ተማሪዎችን በሳይንስ ብሎም በሂሳብ ትምህርት ያላቸውን ፍላጎት ለመጨመር፣ እንደ አስቸጋሪ እና ከባድ የትምህርት አይነት የሚቆጠረውን የሂሳብ ትምህርት በተቻለ መጠን ቀለል ባለ መልኩ እና ከገሃዱ አለም አስተሳስሮ ለተማሪዎች ለማስረጽ እንዲሁም የችግር መፍትሄ ችሎታን በሂሳብ ትምህርት አማካኝነት ማሻሻል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር ሁነኛው አክለውም በሂሳብ ውጤታማ የሆነ ተማሪ በሁሉም የሳይንስ ዘርፎች ስኬታማ ይሆናል ተብሎ ስለሚታሰብ ተማሪዎች ለሂሳብ የትምህርት አይነት ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጡት ይገባል ብለዋል፡፡
በመቀጠልም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ ዳይሬክተር ዶ/ር ነፃነት በይሮ በመክፈቻ ንግግራቸው በአሁኑ ሰአት በአደጉ አገሮች የሚኖሩ ብዙ ኢትዮጵያውያን ሳይንቲስት ሆነው እያየን ነው፤ እናንተም የተሻለ የሂሳብ እውቀት ስላላችሁ ነገ ከነገ ወዲያ በተለያዩ ሀገራት ተመራማሪና ሳይንቲስት እንደምትሆኑ እንጠብቃለን ብለዋል፡፡ ዶ/ር ነፃነት በመጨረሻም በቆይታችሁ ከስልጠናው በተጨማሪ የእርስ በእርስ ተግባቦትና ማህበራዊ ግንኙነታችሁን የሚያጠናከር ጊዜ ይኖራችኋል ሲሉ ለተማሪዎች ገልጸዋል፡፡




