በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቴክስታይል እና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እና በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ በጋራ ለመስራት የሚያስችል የትግበራ ስምምነት ውል ተፈራረሙ። የስምምነቱ ዓላማ በሁለቱ ተቋማት መካከል ያለውን የትብብር ማዕቀፍ ወደ ትግበራ ለማስገባት መመሪያ ማውጣት፣ ኃላፊነቶችን መለየት እና በቅርብ ትብብር እና አጋርነት ለመስራት መሆኑን ሰነዱ ያስረዳል::
በፊርማ ስነስርዓቱም ዶ/ር ፍሬው ተገኘ ዩኒቨርሲቲው የመግባቢያ ሰነድ የሚፈራረመው ይህን ያክል አጋር አለን ለማለት የሚፈራረም አለመሆኑን ገልጸው ዩኒቨርሲቲው ከስምምነት ውጭ ለማሕበረሰቡና ለCተማዋ በርካታ ስራዎችን እየሰራ የሚገኝ ነው ብለዋል:: አሁን በመተግበር ላይ ያለው የባሕር ዳር ከተማ መዋቅራዊ ፕላን በባለቤትነት አዘጋጅቶ ያስረከበበት ሁኔታ መኖሩን ገልፀው ባሕር ዳር ከተማ እስከ 2055 ድረስ የዩኒቨርሲቲ ከተማ፣ በዩኒስኮ የትምህርት ከተማ፣ የቱሪዝም እና ኢንቨስትመንት ከተማ እንድትሆን ዩኒቨርሲቲው እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
ዶ/ር ፍሬው አክለውም ዛሬ ላይ በጣም የምንኮራበት እና ከፖሊ ቴክኒክ ምስረታ አንስቶ ከዲፓርትመንት ጀምሮ በምሰራቅ አፍሪካ አንቱ የተባለው ተቋማችን የኢትዮጵያ ቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሲሆን ከእኛ አልፎ ለሌላው የሚትርፍ ፀጋ ያለው ተቋም ነው፡፡ በመሆንም እንደ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሁሉ ሌሎች ተቋማት የዩኒቨርስቲ ባለሙያዎችን ካልተጠቀሙ የሚፈለገውን እድገት ማግኘት የሚቻል አይደለም ብለዋል፡፡
አቶ እንድሪስ አብዱ የአብክመ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ በበኩላቸው ከግብርናው ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ ኢኮኖሚ ለሚደረገው ሽግግር የ10 ዓመት የልማት ፍኖተ ካርታ የተሰራው በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መሆኑን ገልጸው በዘፈቀደ የሚመራውን የኢንቨስትመንት ስርዓት መስመር በማስያዝ በስድስቱም የልማት ኮሪደሮች እንዴት ልማት መስፋፋት እንደሚቻል በልማት ፍኖተ ካርታው ላይ ላሳየው አስተዋፆ ዩኒቨርሲቲውን አመስግነዋል፡፡
አቶ እንድሪስ አክለውም በክልሉ ካሉ 3346 የአነስተኛ፣ መካከለኛ እና ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች መካከል 844ቱ የቴክስታይልና ቆዳ ኢንዱስትሪዎች መሆናቸውን ገልፀው ቢሮአቸው ከኢትዮጵያ ቴክስታይል እና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር የተፈራረመው የትግበራ ስምምነት ስራዎችን በተግባር የሚሰራ መሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል::
ሁለቱም ተቋማት በጋራ ለመስራት ፍላጎት ካሳዩባቸው መካከል የስራ ማዕቀፎችን በመዘርጋት በጋራ ጉዳዮች ላይ ትምህርት እና ተግባራዊ ስልጠና ማካሄድ:: በኢንዱስትሪ የሚፈለጉ እና ችግር ፈቺ ምርምር እና የልማት ፕሮግራሞችን ማስተዋወቅ:: የሳይንስና ቴክኖሎጂ ግኝቶችን በአካዳሚክ ጆርናሎች በማሳተም የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማካሄድ::: ትምህርታዊ ቁሳቁሶችን እና ሌሎች መረጃዎችን መለዋወጥ እንዲሁም ተማሪዎች ተግባር ልምምድ እንዲያደርጉ መስራት።
በትግበራ ስምምነት ስነስርዓቱ ከኢትዮጵያ ቴክስታይል እና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በኩል የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ የፈረሙ ሲሆን ከአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሰት ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንትን ቢሮ በኩል የቢሮ ኃላፊው አቶ እንድሪስ አብዱ ፈርመዋል፡፡
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የውጭ ግንኙነት ኦፊሰር አቶ እሱባለው ካሳው የዩኒቨርሲቲ እና የአብክመ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ የስራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች በተገኙበት የመግባቢያ ሰነዱን ዝርዝር ሃሳብ አቅርበዋል::