የምስገና እና የዕቅና ፕሮግራም

የምስገና እና የዕቅና ፕሮግራም

የኢትዮጵያ ቴክስታይል እና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ላለፉት ዓመታት በሳይንቲፊክ ዳይሬክተርነት ሲያገለግሉ ለቆዩት ዶ/ር አበራ ከጪ የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ከፍተኛ አመራሮች ፤ የEiTEX ሴኔትና ማኔጂመንት አባላት የምስጋና እና የዕውቅና ፕሮግራም አካሄደ፡፡

የተቋማችን ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር የነበሩት ዶ/ር አበራ ከጪ ለረጅም ጊዜያት በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የአመራርነት ሥራዎች ላይ በታታሪነትና በቅንነት ሲያገለግሉ መቆየታቸዉ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም በአሁኑ ሰዓት ከአመራርነታቸዉ በፈቃዳቸው በመልቀቅ መልካም አርአያ በመሆን ለእረፍት ስለወጡ ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋፅኦ በቴክስታይል ከለሬሽን ከቴክኒካል ረዳትነት እስከ ተባባሪ ፕሮፌሰርነት የሰሩ እና ያሰሩ መሆናቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት የተክስታይል ከለሬሽን ላብራቶሪ በስማቸዉ እንዲሰየምላቸው የEiTEX ሴኔት በ 05/05/2014 ዓ.ም በአካሄደው ስብሰባ ወስኗል፡፡

የኢትዮጵያ ቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ለዶ/ር አበራ ከጪ ዕውቅና ለመስጠት ያበቃው ዋና ዋና ተግባራትም ዶ/ር አበራ በትምህርት ራሳቸውን ከማነፅ ጎን ለጎን በማስተማር ሥራው በተለያየ የትምህርት ማዕረግ ከቴክኒክ ረዳትነት እስከ ተባባሪ ፕሮፌሰርነት በመምህርነትና በተመራማሪነት በማገልገል የነበረውን የመምህራን ዕጥረት በመሸፈን ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ የተለያዩ ኮርሶችን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በትጋት ያስተማሩ ሲሆን በተለይም Theory of Coloration እና Dyes and Auxiliaries ላይ specialize በማድረግ በመስኩ የነበረውን የባለሙያ እጥረት በመፍታት ረገድ የራሳቸውን ትልቅ አሻራ አኑረዋል፡፡

ዶ/ር አበራ በተለያዩ የትምህርት እርከኖችና የትምህርት ማዕረጎች ለዩኒቨርሲቲው ከሰጧቸው አበርክቶዎች በተጨማሪ በተለያዩ አስተዳደራዊ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ተመድበው በማገልገል ለዩኒቨርስቲያችን ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል፡ ከነዚህም መካከል በኢንጅነሪንግ ፋኩልቲ በምርት ማዕከል አስተባባሪነት፣በገቢ ማመንጫ ኃላፊነት፣በቅድመ-ምህንድስና እና ሳይንስ ትምህርት አስተባባሪነት፣በዲንነት፣በተባባሪ ምክትል ፕሪዘዳንትነት ሥራቸውን በትጋትና በብቃት ተወጥተዋል፡፡ በተጨማሪም በኢትዮጵያ ቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የድህረ-ምረቃ፣የቴክኖሎጂ ልማትና የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር ፣የድህረ-ምረቃ ጥናቶችና የፕሮጀክት ልማት ዳይሬክተር፣ከአዳማ ዩኒቨርሲቲ ጋር ባለ ጥምረት የአገር በቀል የድህረ-ምረቃ አስተባባሪ ፣ የEiTEX የልህቀት ማዕከል ተጠሪ፣ የኢትዮጵያ ቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር በመሆን የተጣለባችውን ኃላፊነት በቅንነትና በታማኝነት ፈፅመዋል፡፡

 በመጨረሻም ዶ/ር አበራ ከጪ በፕሮግራሙ ላይ ባደረጉት ንግግር በሃላፊነት ዘመናችው የተቋሙ ማህበረሰብ ላደረገላቸዉ ቀና ትብብር አመስግነው በቀጣይም የአንድ ተቋም ጥንካሬና ውጤታማነት በአንድ ግልሰብ ብቻ ስለማይወሰን ለተቋማችን ጥንካሬና ውጤታማነት ሁላችንም አብረን በአንድነት መስራት እንዳለብን መልክት አስተላልፈዋል፡፡

Share