Covid-19 info

ኮቪድ-19 ምንድን ነው?


የኮሮና ቫይረስ በሽታ (ኮቪድ-19) ሳርስ-ኮቭ 2 (SARS-COV-2) በተሰኘ እና ከዚህ ቀደም ተከስቶ በማያቅ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ የሚመጣ የመተንፈስ ችግር የሚያስከትል ተላላፊ በሽታ ነው። ሳርስ ኮቭ -2 በመባል የሚታወቀው ይህ ቫይረስ የ ኮሮና ቫይረስ ዝርያ ቤተሰብ አንዱ ሲሆንከ 80 እስከ120 ናኖ ሜትር (10-9) የሚለካ በአይን የማይታይ ቫይረስ ነው፡፡
ይህ ቫይረስ ከሌሊት ወፍ ከሚገኘው ሳርስ ኮሮና ቫይረስ ጋር ካለው የ96 በመቶ ቀረቤታ አንፃር ቫይረሱ ከሌሊት ወፍ የተገኘ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ቫይረሱ ወደ ሰው ከመተላለፉ በፊት ሌሎች እንስሳቶች እንደ መካከለኛ የቫይረሱ አስተላላፊ ሊሆኑ ይችላሉ። ይህ ቫይረስ በእንስሳት ውስጥ ከመተንፈሻ አካላት በሽታ በተጨማሪ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ላይ በሽታን ያስከትላል ይሁንና በሰዎች ውስጥ ከቀላል ህመም እስከ ከባድ የመተንፈሻ አካላት ህመም ያሉ በሽታዎችን የሚያስከትል ነው፡፡ ሌሎች የኮሮና ቫይረስ አይነቶች ውስጥ ሳርስ ኮቭ (SARS-COV) እና መርስ ኮቭ (MERS-COV) በመባል የሚታወቁ ቫይረሶች ይገኙበታል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ እነዚህ ቫይረሶች ሳርስ በ 2002 እ.ኤ.አ እና መርስ በ2012 እ.ኤ.አ ብዙ ሰዎችን የያዘ ወረርሽኝ አስከትለው አልፈዋል፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ ከውሃን ከተማ፣ ሁቤይ ክፍለ ሀገር፣ ቻይና መንስኤው ያልታወቀ የሳንባ ምች ህሙማን እንደነበራቸው በታህሳስ 21፣ 2012 ዓ.ም ለዓለም ጤና ድርጅት አሳውቀዋል፡፡ ይሁንና ቫይረሱ ከቻይና አልፎ ሌሎች ሀገራት ላይ በፍጥነት እየተስፋፋ ብዙ ሰዎችን ከመያዛቸውም በላይ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል፡፡ ይህንን መሰረት በማድረግ የዓለም ጤና ድርጅት በሽታው በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሕብረተሰብ ጤና አሳሳቢ ችግር መሆኑን በጥር 21፣ 2012 ዓ.ም አውጇል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ቫይረሱ በብዙ ሀገራት ውስጥ በመሰራጨቱና ብዙ ህዝብን በመያዙ የዓለም የጤና ድርጅት በመጋቢት 2፣2012 ዓ.ም በሽታውን የዓለም ወረርሽኝ (pandemic) እንደሆነ አውጇል፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ ከጥር 18፣ 2012 ዓ.ም ጅምሮ ለኮቪድ-19 የድንገተኛ ጊዜ ዝግጅት እና ምላሽ ማስተባበሪያ ማእከል በማቋቋም ለበሽታው ቁጥጥር ውጤታማነት የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ዝግጅት ስታደርግ ቆይታ የመጀመሪያው በበሽታው መያዙ የተረጋገጠ ሰው በመጋቢት 3፣ 2012 ዓ.ም ሪፖርት ተደርጓል፡፡

መከላከያ መንገዶች


መከላከል ለ ኮቪድ-19 በጣም ውጤታማው ዘዴ ነው ፡፡
1. የመተንፈሻ አካላት በሽታ ምልክት ከሚያሳዩ ሰዎች ጋር የቅርብ ንክኪ አለመኖር፣
2. አይኖን፣ አፍንጫዎን እና አፍዎን ባልታጠበ እጅ ከመንካት ይቆጠቡ
3. የእጅዎን ንጽህና መጠበቅ
4. አልኮል ነክ የእጅ ማጽጃዎችን ወይም ሳኒታይዘሮችን ይጠቀሙ
5. ከእርሻ እና ከዱር እንስሳት ጋር ያልተጠበቀ ግንኙነት ይቀንሱ
6. ቁሳ ቁሶችን ንጽህና መጠበቅ መደበኛ የህይወት ዘይቤዎች መደረግ አለባቸው።
7. በቂ እረፍት እና በቂ የቫይታሚንሲ፣ ዲ እና ኢ ጨምሮ የአኗኗር ዘይቤን በማስተካከል በቫይረሱ የመቋቋም ችሎታውን ከፍ እንደሚያደርጉ ይመከራል፡፡

ህክምና


እስካሁን ድረስ ለኮቪድ-19 ውጤታማ የሆነ ሕክምና ሆነ ክትባት የለም፡፡ በአሁኑ ወቅት የሚሰጡ አብዛኞቹ ሕክምናዎች የበሽታውን ምልክቶች ለማስታመም የሚደረጉ ድጋፍ ሰጪ ሕክምናዎች ናቸው፡፡ እንደ የደም ግፊት መቀነስ፣ከባድ የኩላሊት ጉዳት፣ ከባድ የልብ ህመም፣ ከነርቭ ስርዓት ጋር የተያያዙ ችግሮችን እና እንደ ኢንፌክሽን ያሉ የበሽታው ጎንዮሽ ችግሮች እንደ አስፈላጊነቱ ሊታከሙ ይችላሉ። ከሌሎች የፀረ-ቫይረስ መድሃኒቶች ጋር ክሎሮኪንን የሚባል የወባ መድሀኒት ጨምሮ የተለያዩ ምርመራዎች ላይ ያሉ መድሀኒቶች አሉ፡፡በአገራችን ከባህላዊ ሕክምና ጋር ተያይዞ ከዘመናዊ መድኃኒት ጋር በማጣመር ሙከራ ተጀምሯል፡፡ ሆኖም በአሁኑ ሰዓት የኮቪድ-19 በሽታን ለመከላከልም ሆነ ለመፈወስ የሚውል መድሃኒት ስለሌለ ለዚህ ተብሎ ማንኛውንም መድሃኒት መጠቀም አይመከርም፡፡
1. የእጅዎን ንጽህና ይጠብቁ
2. እጅዎን እንዴት እና መቼ እንደሚታጠቡ ይወቁ
3. ሳሙና እና ውሃን ይጠቀሙ
4. እጆችዎን ቢያንስ ለ40 ሰከንዶች ይታጠቡ
እጅዎን ለመታጠብ የዓለም ጤና ድርጅት ቴክኒኮችን / ደረጃዎችን (ይመልከቱ) ይጠቀሙ ወይም አብዛኛውን ጊዜ የሚረሱትን የጣትዎን መገጣጠሚያ፣ የእጅ መዳፍ፣ የጣት ጫፍ እና የእጆችን ጀርባ መታጠብዎን ያስታውሱ። ወደ ህዝባዊ ቦታዎች ከሄዱ በኋላ፣ ካሳሉ ወይም ካስነጠሱ በኋላ፣ ፊትዎን ከመንካትዎ በፊት፣የተበከሉ እቃዎችን ከነኩ በኋላ፣ ከማስነጠስዎ ወይም ካሳለዎት በኋላ፣ መጸዳጃ ቤት ከተጠቀሙ በኋላ፣ ምግብ ከማዘጋጀት ወይም ምግብ ከመመገብዎ በፊት፣ በተለይም ከእንስሳት ጋር ንክኪ ካደረጉ በኋላ እና ሌሎችን ከመንከባከቦ በፊት እና በኋላ እጅዎን ይታጠቡ፡፡
• አልኮል ነክ የእጅ ማጽጃዎችን ወይም ሳኒታይዘሮችን ይጠቀሙ
• የንፅህና አጠባበቅ ይዘቱ ቢያንስ 60% የአልኮል መጠን ያለው መሆኑን ያረጋግጡ
• እንደ እጅን በሳሙና እና ውሃ መታጠብ እርምጃዎች እጆችዎን በተመሳሳይ መንገድ ይሹት ወይም የእጅዎን ሁሉንም ገጽታዎች መሸፈንዎን ያስታውሱ
• አልኮሉ ከእጅዎት በመትነን እስኪደረቅ ድረስ እጅዎትን ይሹት


አልኮል ወይም ሳሙና ቫይረስን እንዴት ይገድላል?


የኮሮና ቫይረስ ሽፋን ከፊል ቅባትነት ከፊል ፕሮቲንነት ካለው ንጥረ ነገሮች የተሰራ ሲሆን እንደነዚህ ያሉት ቫይረሶች በቀላሉ እቃዎች ላይ እና ሰውነታችን ላይ መለጠፍ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን እጃችንን በውሃ ብቻ ስንታጠብ ውሃው ቅባትነት ያለውን የቫይረሱን መሸፈኛ ውስጥ መግባት ስለማይችል ከላይ በማለፍ ሳያስወግደው ያልፋል፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ቫይረሱን የሚሸፍነው ቅባትነት ያለው ንጥረ ነገር ከውሃ ጋር ስለማይዋሃድ ነው፡፡ ነገር ግን ሳሙና ቅባትነት ካላቸው ንጥረነገሮች ጋር መዋሀድ ስለሚችል እጃችንን በሳሙና በምንታጠብበት ጊዜ ቅባትነት ያለው የኮሮና ቫይረስ ሽፋን ከሳሙናው ጋር በመዋሀድ ወደ ውሃው እንዲበተን ያደርጋል፡፡ በመቀጠል በውሃ በሚታጠቡበት ወቅት የቀረውን በውሃ የሚዋድ የቫይረስ ክፍል በቀላሉ ማስወገድ ይቻላል፡፡ ነገር ግን ይህ ሂደት ማለትም ሳሙናው ቅባትነት ያለውን የቫይረሱን ሽፋን ጋር አብሮ እስኪዋሃድ ድረስ ቢያንስ 40 ሰከንዶችን ይፈጃል፡፡
1. እቃዎችን እንዴት እንደሚያፀዱ ይወቁ?
2. የተበከሉ ቦታዎችን ለማፅዳት ከውሃ ጋር በተዋሀደ በረኪና ከዚያም በሳሙና እና በውሃ ይጠቀሙ
3. እቃዎችን ሲያጸዱ የማጽጃ ጓንቶችን ይጠቀሙ
4. እንደ መጸዳጃ ቤት፣ መታጠቢያ ገንዳዎች፣ ጠረጴዛዎች፣ በሮች፣ ቁልፎች፣ ስልኮች፣ የመኪና በሮች፣ የመቀመጫ ቀበቶዎች እና የቁልፍ ሰሌዳዎች ያሉ ንክኪ የሚበዛባቸውን እቃዎችን ያፅዱ፡፡
5. እቃዎችን ለማፅዳት አልኮል የሚጠቀሙ ከሆነ የአልኮል ይዘት 70% መሆኑን ያረጋግጡ።
6. ለህክምና እንክብካቤ ምክር እና / ወይም እርዳታ ለማግኘት በስልክ ቁጥር 8335 ወይም 952 ነጻ መስመር ላይ ይደውሉ፡፡
በኮቪድ-19 የታመመን ሰው ለመንከባከብ ምን ማድረግ አለብዎት?
የኮቪድ-19 ምልክቶች ያሉበትን ሰው የሚንከባከቡ ከሆነ የሚከተሉትን ማድረግዎን ያስታውሱ
1. የታመመ ሰው ለብቻው እንዲለይ የተለየ ክፍል ያዘጋጁ
2. በሚያስሉበት ወይም በሚያስነጥሱበት ጊዜ አፍ እና አፍንጫቸውን እንዲሸፍኑ ለበሽተኞች ተገቢ የሆነ የግል መከላከያ መሳሪያ ያቅርቡ
3. የሚቻል ከሆነ የተለየ መታጠቢያ ቤት ያዘጋጁ። ይህ የማይቻል ከሆነ እና መታጠቢያ ቤቱን ከሌሎች የቤተሰብ አባላት ጋር በጋራ የሚጠቀሙ ከሆነ ከአገልግሎት በኋላ ለማፅዳትና ተገቢውን ዘዴ ይጠቀሙ፡፡
4. ለታማሚው እንክብካቤ በሚያደርጉበት ጊዜ ሁሉ ለአንድ ጊዜ አገልግሎት ብቻ የሚውሉ የህክምና ጓንቶችን ይጠቀሙ
5. ለምግብነት የሚጠቀሙባቸውን ዕቃዎችን ጓንቶችን በመጠቀም በሞቀ ውሃ እና በሳሙና ይጠቡ
6. የተጠቀሙበትን ጓንቶች፣ የፊት ማስኮች፣ የተረፈ ምግብ እና የመሳሰሉትን የተበከሉ ቁሳቁሶችን ለማስወገድ የቆሻሻ መጣያ ይለዩ፡፡
7. የመከላከያ እርምጃዎችን በጥብቅ ይለማመዱ
8. የግል እቃዎችን ከማጋራት ይቆጠቡ እንዲሁም እቃዎችን ያጽዱ


ከኮቪድ-19 ማገገም


በኮቪድ-19 የሚያዙት አብዛኛዎቹ ሰዎች ከሰውነታቸው ውስጥ ቫይረሱን ማስወገድ እና ማገገም ይችላሉ።አብዛኛዎቹ ምልክቶች በ 10 ቀናት ጊዜ ውስጥ የሚቀንሱ ሲሆን ታማሚዎቹ የበሽታውን ምልክት ባሳዩ ከ 2 እስከ 4 ባሉት ቀናት ውስጥ የሚያደርጉት ምርመራ ቫይረሱ መኖር አለመኖሩን ማረጋገጥ ሲቻል፣ በራጅ የበሽታውን መኖር ለማረጋገጥግን እስከ 7 ቀናት ሊወስድ ይችላል፡፡ በዚህ በሽታ የተያዙ ሰዎች ቫይረሱ ከሰውነታቸው ሙሉ በሙሉ እስኪጠፋ የሚውስደው ጊዜ ከህመማቸው ለማገገም ከሚውስደው ጊዜ ይረዝማል። በጽኑ የታመሙ ህመምተኞች ከሌሎች ጋር ሲወዳደሩ ቫይረሱ ከሰውነታቸው እስኪወገድ ረዘም ያለ ጊዜ ይወስዳል፡፡ ስለዚህም አሁን አገራችን ላይ ባለው መመሪያ መሰረት ታካሚዎች ከበሽታው ካገገሙ በኋላ ለጥቃቄ ሲባል ለ14 ቀን የህክምና ክትትል በለይቶ ማቆያ ይደረግላቸዋል፡፡
የለይቶ ማቆያ ህክምና እና ለይቶ ማቆያ (ቀሳ)
ከኮቪድ-19 በሽታ ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ ያላቸውን ሰዎች ማፈላለግ ፣ የለይቶ ማቆያ ክፍል እና የለይቶ ህክምና መስጫ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ዋና እርምጃዎች ናቸው።
የንክኪ ፍለጋ የሚደረግላቸው ሰዎች ለቫይረሱ ተጋልጠዋል ተብሎ ለሚታሰብ ሰዎች ነው፡፡ አንድ ሰው የግል መከላከያ መሳሪያዎችን ሳይጠቀም ወይም ዝግ በሆነ አካባቢ ውስጥ ሆነው ለታካሚው ቀጥተኛ እንክብካቤ በሚሰጥበት ጊዜ ሰዎች የቅርብ ንክኪ አላቸው ልንል እንችላለን፡፡ ከታካሚው ጋር የቅርብ ንክኪ ከነበራቸው ጊዜ አንስቶ ለ 14 ቀናት ያህል በለይቶ ማቆያ ክፍል ክትትል ይደረጋል። የለይቶ ማቆያ ክፍል የበሽታ ምልክት ለማያሳዩ ሲሆን ከበሽተኞች ጋር ንክኪ ያላቸውን ሰዎች እንቅስቃሴዎች በመግታት የበሽታውን ስርጭት ቀደም ብሎ ለመያዝ እና ለመቆጣጠር ይጠቅማል፡፡
• በለይቶ ማቆያ ያለ ወይም የቅርብ ንክኪ ያለውን ሰው ማወቅ የሚገባው ለምንድነው?
• በለይቶ ማቆያ መለየት ወይም ንክኪ መኖሩ ግለሰቡ በበሽታው ተይዟል ማለት አይደለም
• በለይቶ ማቆያ መለየት ለራስ እና ለሚወዷቸው ሰዎች ሲባል የሚደረግ ሂደት ነው
• በለይቶ መቆያ ያለ ሰው ምልክቶች ሊያሳዩ ስለሚችሉ በሥነልቦና መዘጋጀት አለባቸው
• የመከላከያ ዘዴዎችን አዘውትረው ያድርጉ (የመከላከያ ዘዴዎችን ለማየት ይህንን ይጫኑ)
• እንደአስፈላጊነቱ የፊት ጭንብል ይጠቀሙ
• በተለይ በከባድ የበሽታው ምልክቶች ለመጠቃት ተጋላጭ ከሆኑ ሰዎች ጋር ንክኪዎን ያስወግዱ
• ክትትል ለሚያደርጉሎት ቡድን ትክክለኛ መረጃ መስጠት አስፈላጊ ነው
www.ephi.gov.et, የተወሰደ
For further updated information, please click Covid-19 Updates and EPHI-Ethiopia Covid info. Addistional reading also available.